የኩዊንስ ሱፐርማርኬት ቅርንጫፎችን 28 ለማድረስ እየሰራ መሆኑን ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ አስታወቀ

የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ አካል በሆነው ኩዊንስ ሱፐርማርኬት ከሸቀጣ ሸቀጥ በተጨማሪ የእህት ድርጅቶች ምርት ለሽያጭ እየቀረበበት ይገኛል፡፡

በአሁኑ ሰአት የኩዊንስ ሱፐርማርኬት ቅርንጫፎች 8 ሲሆኑ በቅርብ ጊዜያት ውስጥ 28 ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ሰኢድ መሀመድ ተናግረዋል፡፡

አቶ ሰኢድ መሀመድ በኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 ሬዲዮ በሚተላለፈው የኢትዮ የንግድ እና ኢንቨስትመንት መድረክ እንደገለጹት ባለፈው የ2014 ዘመን መለወጫ እና መስቀል በዓላት የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ አካል ከሆነው ኤልፎራ አግሮ ኢንደስትሪስ የቀረቡ በአጠቃላይ ከ33 ሺህ በላይ ዶሮ በህይወት ፤ ከ20 ሺህ ኪሎ ግራም በላይ የተበለተ ዶሮ ፤ ከ450 ሺህ በላይ እንቁላል ፤የበግ እና ከ100 በላይ በሬ ታርዶ ስጋው በኩዊንስ ሱፐርማርኬት በኩል ለሽያጭ ቀርቧል፡፡

በተለይም በአዲስ ዓመት የቤት ቁሳቁስ መቀየር የተለመደ መሆኑን ያነሱት አቶ ሰኢድ የኩይንስ እህት ድርጅት በሆነው ዋንዛ ፈርኒሺንግ ኢንደስትሪ የተሰሩ ሶፋ ፤ አልጋ እና ሌሎች የቤት እቃዎች በተመጣጣኝ ዋጋ በሱፐርማርኬቶቹ ለሽያጭ መቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ወቅቱ ወላጆች ለልጆቻቸው የትምህርት መሳሪያዎችን የሚሸምቱበት እና የትምህርት ዘመኑም የሚጀመርበት እንደመሆኑ የኤሊኮ ምርት የሆኑት የቆዳ ውጤቶች እንደ ቦርሳ ፤አልባሳት እና ጫማ ያሉ ምርቶች መቅረባቸው ተገልጿል፡፡

ሌሎች የትምህርት መሳሪያዎችም በኩዊንስ ሱፐርማርኬት በተመጣጣኝ ዋጋ መቅረባቸውን የገለጹት አቶ ሰኢድ ሸማቾች በተመቻቸው ቀን ባቅራቢያቸው በሚገኝ ቅርንጫፍ እየሄዱ የሚፈልጉትን ምርት መገብየት የሚችሉ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡