የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ (CEO) አቶ ጀማል አህመድ የተለያዩ ፕሮጄክቶችንና የእርሻ ኢንቨስትመንቶችን ጎበኙ፡፡

ዋና ስራ አስፈጻሚው ከታህሳስ 26 – 28 ባሉት ቀናት በእርሻና አግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ የተሰማሩትን በሓ ላንድ አግሮ ኢንዱስትሪ፣ ውሽ ውሽ ሻይ ልማት ድርጅት፣ በበቃ ቡና ልማት ድርጅትና ጎጀብ እርሻ ልማት ድርጅትን ጎብኝተዋል፡፡

ከአቶ ጀማል ጋር የአራቱ ዘርፎች ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚዎች እና የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕን የቡና ምርት ትልቁ ገዢ የሆነው የኒውማን ካፌ ግሩፕ (Neumann Kaffee Gruppe – NKG) የኢትዮጵያ ተወካይ በጉብኝቱ ተገኝተዋል፡፡

አቶ ጀማል በዚሁ ጉብኝታቸው ከየድርጅቶቹ ማኔጅመንትና ከሰራተኛ ማህበር አባላት ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡ በዚሁ ወቅት የእርሻ ልማቱን በተመለከተ ለተነሱ ጉዳዮች ውሳኔና የስራ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡

ዋና ስራ አስፈጻሚው ከጥር 13 – 14 ቀን 2013 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት ደግሞ የላይኛው አዋሽ አግሮ ኢንዱስትሪን ጎብኝተዋል፡፡ በዚህም ጉብኝታቸው የእርሻውን የተለያዩ ማሳዎች፤ የቲማቲም፣ የብርቱካን፣ የማንጎና የፓፓያ እርሻዎችን፣ የማቀነባበሪያ ፋብሪካውንና፣ የቋሚ ሰብል ችግኝ ማዘጋጃዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡

በዚህም ወቅት ያረጁ የፍራፍሬ ዛፎች በ5 ዓመታት ጊዜ ውስጥ በየዓመቱ በ20% እንዲተኩ፣ ሰራተኞች በባለቤትነት መንፈስ ተግተው እንዲሰሩ መመሪያ ተሰጥቷል፡፡

የላይኛው አዋሽ አግሮ ኢንዱስትሪ፤ ማህበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አኳያ አዋሳኙ ለሆኑ አራት ወረዳዎች መሰረተ ልማት ማስፋፊያ በጀት መድቦ ድጋፍ የሚያደርግ ሲሆን፤ በአጠቃላይ ከሰባት ሺህ በላይ ለሆኑ ሰዎች ጊዜያዊና ቋሚ የስራ እድል መፍጠሩ ይታወቃል፡፡