ኩይንስ ሱፐርማርኬት 8ኛውን ቅርንጫፉን ሪሐብ በሚል ስያሜ በአዲስ አበባ ከተማ ሰፈረ-ሰላም አካባቢ አስመረቀ፡፡

ኩይንስ ሱፐር ማርኬት በማህበረሰቡ ላይ እየተፈጠረ ያለውን የዋጋ ንረት ተፅዕኖ በማቃለል ረገድ ሚናውን በመወጣት ላይ እንዳለ ሱፐርማርኬቱን መርቀው የከፈቱት የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አህመድ ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ ጀማል ገለጻ ኩይንስ እንደ ቤተሰብ የአግሮ ኢንደስትሪ፣የእርሻና የፋብሪካ ውጤቶች ያለምንም ደላላና ጣልቃ ገብነት በቀጥታ ለህብረተሰቡ የሚደርሱበት አውታር በመሆኑ ሃገራዊ ፋይዳው ላቅ ያለ ነው፡፡

በምርቃት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ይታያል ደጄኔ በበኩላቸው ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በክፍለ ከተማው ያሉ ክፍተቶችን ለመሸፈን እያደረገ ያለው ጥረት የሚያስመሰግን ነው ብለዋል፡፡

በከተማዋ ካሉ አስራ አንዱም ክፍለ ከተሞች በገቢ ደረጃ በጣም ፈታኝ የሆነ አኗኗር እየኖረ ላለ ህብረተሰብ ኩይንስ እንደቤተሰብ መከፈቱ አማራጮችን እንደሚያሰፋ አቶ ይታያል ተናግረዋል፡፡

ይህንን ደግሞ ሚደሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ይፋ ባደረገው ሸገር ዳቦ ፕሮጀክት በኩል ለወጣቶች የስራ እድል በመፍጠር ጭምር ውጤቱን ማየታቸውን ነው አቶ ይታያል የገለጹት፡፡በክፍለ ከተማው የዚህ ዓመት የኢደል ፊጥር ሥጦታ በመሆን ተመርቆ የተከፈተው አሙዲ የምገባ ማዕክል ለብዙዎች እፎይታን እየሰጠ በመሆኑም ለሼህ ሙሀመድና ለአቶ ጀማል ታላቅ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ክፍለ ከተማው እነዚህን ባለ ብዙ ፋይዳ ፕሮጀክቶች ውጤታማ እንዲሆኑ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግ አቶ ይታያል ቃል ገብተዋል፡፡

በሌላ በኩል ሚደሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በሚያከናውናቸው ተግባራት መንግስት ድጋፍ እያደረገ መሆኑንና ተቋማቸውም ስራዎቹን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ጀማል ተናግረዋል፡፡

በግሩፑ ስር ያሉት ኩባንያዎች ምርታማነት በተቋሙ ውሥጥ ከመጣው ለውጥና ከተደረገው የአደረጃጀት ማስተካካያ በኋላ ከፍተኛ እምርታ ማሳየቱን የተናገሩት አቶ ጀማል፤ይህንንም በአብነት አስረድተዋል፡፡

እንደ አቶ ጀማል ገለጻ ኤልፎራን ከመረከባችው በፊት ለዚያውም እየተቆራረጠ በሳምንት 4,000 ዶዎች ለኩይንስ ይቀርቡ ነበር፡፡አሁን ግን በቀን 2,000 ዶሮዎችን የማቅረብ አቅም ላይ ደርሷል፡፡በዚህም መሰረት በሳምንት 14,000 ዶሮች ለሁሉም የኩይንስ ሱፐርማርኬት ቅርንጫፎች ይከፋፈላሉ፡፡ይህም በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር 350 በመቶ ይበልጣል ማለት ነው፡፡ ይህ የሆነው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ እንቁላል፣ወተት፣ሽንኩርት፣ቲማቲምና ሌሎች ምርቶችም ላይ ተመሳሳይና አስገራሚ የምርት አቅርቦት እድገቶች መመዝገባቸውን የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አህመድ ገልጸዋል፡፡

የኩይንስ ሱፐር ማርኬት ዋና ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሰሚራ ሸረፋ በበኩላቸው አዲስ በተከፈተው ሪሐብ ቅርንጫፍ ውስጥ በሁሉም ቅርንጫፎች ያሉ የምርት ዓይነቶች በሙሉ በተመጣጣኝ ዋጋ መቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡

የአካባቢው ነዋሪዎችም በሰፈሩ ውሥጥ ምንም ዓይነት መሰል የንግድ ተቋም ባለመኖሩ ሩቅ ቦታ በመሄድ ይገዙ እንደነበር ገልጸው የኩይንስ ሱፐር ማርኬት በአቅራቢያቸው በመከፈቱ ታላቅ ደስታ እንደተሰማቸው አስረድተዋል፡፡

ኩዊንስ ሱፐርማርኬት አዲስ የተከፈተውን ሪሐብ ጨምሮ ቅርንጫፎቹን 8 አድርሷል፡፡እነርሱም፡-

  • ጦር ሀይሎች አሙዲ ፕላዛ
  • ብስራተ ገብርኤል ሎሊ ህንጻ ሎሊ ቅርንጫፍ
  • መቻሬ ሜዳ ሁዳ ቅርንጫፍ
  • ሰፈረ ሰላም  ሪሐብ ቅርንጫፍ
  • መካኒሳ ኢትዮ አግሪሴፍት ግቢ ሳራ ቅርንጫፍ
  • ላምበረት/ጉርድ ሾላ ኤልፎራ ግቢ/ ሩቂያ ቅርንጫፍ
  • ቃሊቲ ሸገር ዳቦ ግቢ ፈጡም ቅርንጫፍ
  • ስታዲየም ናኒ ህንጻ ናኒ ቅርንጫፍ እና በካዛንቺስ ቶታል አካባቢ የሚገኙ መሸጫዎች ናቸው፡፡

የሚደሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ አካል የሆነው ኩይንስ ሱፐር ማርኬት በአዲስ አበባ ከተማ የሚከፍታቸውን ቅርንጫፎች ብዛት 28 ለማድረስ እየሰራ መሆኑ ይታወቃል፡፡

 

በሰኢድ መሀመድ

በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ

 

                           ኩዊንስ እንደቤተሰብ