ኤልፎራ አግሮ ኢንደስትሪስ የመልጌ ወንዶ የሥጋና የአትክልት ሾርባ ማቀነባበሪያ የማስፋፊያ ፋብሪካን አስመረቀ፡፡

የማስፋፊያ ፋብሪካው መገንባት ቀድሞ የነበረውን የማምረት አቅም በእጥፍ እንደሚያሳድገው ተገልጿል፡፡

በሲዳማ ክልል በወንዶ ወረዳ የሚገኘው መልጌ ወንዶ የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ የአትክልት ሾርባን በማምረት ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ በ1928 ዓ.ም የተመሰረተው ይህ ፋብሪካ በተለይም በፀጥታ ዘርፍ ለተሰማሩ ዜጎች ምርቱን በማቅረብ ይታወቃል፡፡በ1990 ዓ.ም ከመንግስት ወደ ኤልፎራ አግሮ ኢንዱስትሪ የተዛወረው ይህ ፋብሪካ በቀን 90 ሺህ ጣሳ የማምረት አቅም ነበረው፡፡አሁን የተመረቀው የማስፋፊያ ፋብሪካ ስራ በመጀመሩ ምርቱን በቀን ከ160 ሺህ ጣሳ በላይ ማሳደጉ ተገልጿል፡፡ የምርቃት ሥነ ስርዓቱን የከፈቱት የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አህመድ እንደተናገሩት ፋብሪካው ምርቱን  ከመጨመርና አመራረት ሂደቱን ከማዘመን ባሻገር ቀደም ሲል ሲያመርተው ከነበረው የአትክልት ሾርባ በተጨማሪ የሥጋና የምንቸት አብሽም ያመርታል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድርን ወክለው የተገኙትና የክልሉ ፕሬዚዳንት የማህበራዊ ዘርፍ ልዩ አማካሪ አቶ ተሰማ ዲማ በበኩላቸው ፋብሪካው በተለይም በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ሚናውን ለማሳደግ እያደረገ ያለውን  ጥረት አድንቀዋል፡፡

ኤልፎራ አግሮ ኢንደስትሪስ የመልጌ ወንዶ የሥጋና የአትክልት ሾርባ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ  ከሁለት ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰራተኞች የስራ ዕድል የፈጠረ  ፋብሪካ ሲሆን አዲሱ ፋብሪካ ወደስራ በመግባቱም ሰራተኞች ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በበርካታ ዘርፎች ተሰማርቶ ከሚያደርገው የልማት ሥራዎች ጎን ለጎን በየአካባቢው የማህበራዊ ኃለፊነቱን በመወጣቱ ህዝቡም በተለያዩ ጊዚያት በኔነት ስሜት ከተቋሙ ጎን መቆሙን አቶ ጀማል ተናግረዋል፡፡የክልሉ መግስትም ግሩፑ ያደረጋቸውን ተግባራት አበረታች መሆናቸውን ገልጾ ይህንኑ አጠናክሮ እንዲቀጥል አስገንዝቧል፡፡

ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በሲዳማ ክልል በቀጣይ ሪዞርቶችን ጨምሮ ሌሎች ትልልቅ የልማት ሥራዎችን ለመስራት ማቀዱንም ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ጀማል አህመድ ተናግረዋል፡፡

ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ከ40 በላይ ድርጅቶችን ያቀፈና ከ65 ሺህ ለሚልቁ ዜጎች የስራ እድል የፈጠረ ተቋም ነው፡፡

ሰኢድ መሀመድ

በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ