በሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ ስም የተሰየመ የምገባ ማዕከል ተመረቀ

በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ እና በዳሽን ባንክ ወጪ የተገነባውና “ተስፋ ብርሃን አሙዲ የምገባ ማዕከል” የተሰኘ በቀን አንድ ጊዜ እንኳን መመገብ የማይችሉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን የሚመግብ ማዕከል ተመርቀ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ፣ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ፣ ተክለ ሃይማኖት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የተገነባው ይህ ማዕከል በከተማዋ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የክብር እንግዳነት ተመርቋል፡፡ የምርቃት ሥነ-ሥርዓቱ ሀሙስ ግንቦት 5 ቀን 2013 ከተከበረው የኢደል ፊጥር በዓል ጋር በደማቅ ሁኔታ ተከናውኗል፡፡

የምገባ ማእከላቱን መክፈት ያስፈለገው በተለያየ ምክንያት ለማህበራዊ ችግር የተጋለጡ ወገኖችን ለመመገብ በማሰብ መሆኑን ምክትል ከንቲባዋ አስረድተዋል::

ችግሩ የሁሉም ኢትዮጵያዊ በመሆኑ መፍትሄውንም በጋራ ማምጣት በማስፈለጉ በልዩ ሁኔታ የምገባ ማዕከላቱን በ5 የተመረጡ ክፍለ ከተሞች ለመክፈት እየተሰራ መሆኑንም አክለው ገልጸዋል፡፡

ወ/ሮ አዳነች “ዜጎች የእለት ጉርሳቸውን አጥተው ከቆሻሻ ላይ ምግብ እያነሱ ሲመገቡ ማየት የዜግነት ክብርን የሚነካ ነው” ካሉ በኋላ፤ ይህንን ችግር ለመቅረፍ የምገባ ማዕከል ለመስራት የፕሮጀክቱን ሃሳብ ለባለሀብቶች ባጋሩበት ወቅት ፈጥነው ምላሽ ለሰጡት የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ ለአቶ ጀማል አህመድና ለግሩፑ ሰራተኞች አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡

ማዕከሉ ለዚህ እንዲበቃ ላሳዩት ቁርጠኝነትና በሃገር ልማት ላበረከቱት አይተኬ ሚና የሚድሮክ ሊቀ-መንበር ሼህ ሙሀመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ አለማመስገን ንፉግነት እንደሆነ ወ/ሮ አዳነች በዚሁ ወቅት ተናግረዋል፡፡

የክበር እንግዳዋ ክብርት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ማዕከሉን ለገነቡትና ለሚመሩት አካላትም ምስጋናና የዋንጫ ሽልማት አበርክተዋል፡፡

የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አህመድ በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ህንፃ መገንባት ብቻ ሳይሆን በልተው ማደር የማይችሉ አረጋዊያንን፣ የጎዳና ተዳዳሪ ህጻናትንና ዝቅተኛ የህብረተሰብ ክፍሎችን በዚህ ማዕከል በዘላቂነት በቀን ለአንድ ጊዜ ለመመገብ ከዳሽን ባንክ ጋር ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡

“ይህን ማዕከል የተለየ የሚያደርገው ስያሜው ዛሬ አብረውን ባይኖሩም በደግነታቸውና በመንፈስ ሁሌም ከእኛ ጋር ባሉት ሼህ ሙሐመድ በስማቸው በመሆኑ ደስታችንን እጥፍ ድርብ ያደርገዋል፡፡” ሲሉ የግሩፑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አህመድ አስረድተዋል፡፡

አቶ ጀማል አክለውም ሼህ ሙሀመድ ካሉበት ሆነው ለመላው ኢትዮጵያውያን ሰላምን፣በተለይም ለሙስሊሞች የኢደል ፊጥር በረካን እንዲጎናጸፉ የሚል መልዕክት ማስተላለፋቸውን ተናግረዋል፡፡

ማዕከሉ ሁለት ሺህ የሚደርሱ ሰዎችን መመገብ የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል፡፡

ማዕከሉ በዘላቂነት ከሚያቀርበው የምግብና ቁሳቁስ ድጋፍ በተጨማሪ ለምገባው አገልገሎት ለሚሰጡ በርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን፤ በክፍለ ከተማው ተመልምለው የምገባ መርሃ ግብሩ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተደረጉትና የዕለት ጉርስ የሌላቸው ነዋሪዎችም ስለተደረገላቸው ሁሉ በማመስገን ደስታቸውን ገልፀዋል፡፡ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ከሚያከናውናቸው ገበያን የማረጋጋት እና ጥራት ያላቸውን ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ከማቅረብ ጎን ለጎን ማህበራዊ ኃላፊነቶችን በመወጣት ረገድም በርካታ ተግባራትን እያካነወነ መሆኑ ይታወቃል፡፡.