ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የገዛትን "ኪንግ ኤር 360" የተሰኘች ዘመናዊ አውሮፕላን ተረከበ

ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካው ቴክስትሮን ቢችክራፍት (Textron Beechcraft) ኩባንያ የተመረተችና በአይነቷ የተለየች “ኪንግ ኤር 360” አይሮፕላን ወደ ኢትዮጵያ አስገብቷል፡፡በትላንትናው እለት ጥር 1 ቀን 2014 ዓ.ም በቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የግሩፑ አመራሮችና እንግዶች በተገኙበት አቀባበል የተደረገላት ይች አውሮፕላን በግሩፑ ስር በአየር ትራንስፖርት ንግድ ላይ በተሰማራው በትራንስ ኔሽን ኤርዌይስ ኃ.የተ.የግ.ማ. (ቲ ኤን ኤ) ወደ ስራ እንደምትገባና በዘርፉ ለሀገራችን አስተዋፅኦ እንደምታደርግ ተገልጿል። በፕሮግራሙ ላይ ለተገኙት እንግዶች ንግግር ያደረጉት የቲ ኤን ኤ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አሚር አብዱልወሀብ እንደተናገሩት አውሮፕላኗ በአፍሪካ አህጉር ውስጥ በግሉ ዘርፍ ባለቤትነት ስትገዛ የመጀመሪያ ከመሆኑም ባሻገር በሀገሪቱም ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ውጪ አዲስ አውሮፕላን ተገዝቶ ሲገባ ቀዳሚዋ ነች ።እንደ አቶ አሚር ገለጻ በአይነቷ የተለየችዉ ይህቺ አውሮፕላን ልዩ ከሚያደርጓት ባህሪያት መካከል ምቾትና እና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላት መሆኑ ነዉ።ዋና ስራ አስኪያጁ እንዳመለከቱት ነዳጅ ቆጣቢነትም ሌላ መገለጫዋ ሲሆን በሰዓት እስከ 561 ኪሎ ሜትር የመብረር አቅም አላት፡፡የቢችክራፍት ኪንግ ኤር 360 ቱርቦፕሮፕ አውሮፕላኗ ተገጣጣሚ የውስጥ ክፍሎች እንዳሏት የተገለጸ ሲሆን ለ8 ቪአይፒ መንገደኞች ወይም 13 ቪአይፒ ላልሆኑ መንገዶኞች መቀመጫዎቿ እንደየአሰፈላጊነቱ እየተቀያየረ ጥቅም ላይ ሊዉል ይችላል። በተጨማሪም ለጭነት አገልግሎት እንዲውል ተደርጎ ሊዋቀር የሚችል ሲሆን በአንድ ጊዜ እስከ 2000 ኪሎ ግራም ክብደት ያላቸው እቃዎችን የማጓጓዝ አቅም አላት፡፡እንደአስፈላጊነቱም ለህሙማን የአየር አምቡላንስ አገልግሎት መስጠት በሚያስችል መልኩ ወንበሮቿን አንስቶ ስትሬቸር በመተካት ተልዕኮ መወጣት በሚያስችል መልኩ የተፈበረከች እንደሆነችም ገልጸዋል፡፡ዘመናዊነትን የተላበሰችዉ አውሮፕላኗ የግሩፑ አካል ወደሆነዉ ወደ ቲኤንኤ በመቀላቀሏ ኩባንያው ለደንበኞቹ የሚሰጠውን አገልግሎት እንደሚያሳድግ ይታመናል።በአቀባበል ስነ ስርዓቱ ላይ የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጀማል አህመድ፣ የግሩፑ ከፍተኛ አመራሮች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።ትራንስ ኔሽን ኤርወይስ (ቲ ኤን ኤ) በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝ ቻርተር የአውሮፕላን ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥና የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ አንደኛው ድርጅት ነው፡፡ ድርጅቱ ከንግድ ሚኒስቴር የቢዝነስ ኦፕሬቲንግ ሰርተፍኬት እና ከኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን የአየር ኦፕሬተር ሰርተፍኬት በመቀበል እ∙አ∙አ በ2004 ዓ.ም የተመሰረተ ነው። የኩባንያው ዋና አላማም አስተማማኝ የመንገደኞች እና የካርጎ አየር ትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት ነው።ቲኤንኤ በአሁኑ ጊዜ ሶስት አውሮፕላኖች ያሉት ሲሆን፤ ሁለት ዳሽ-8-200 አውሮፕላኖች ET-ALX & ET-AKZ ሆነው የተመዘገቡ እና አንድ ኪንግ ኤር 360፤ ET-AYW ሆና የተመዘገበችው አዲሷ አውሮፕላን ናቸው።