ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ እና ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አብሮ ለመስራት ስምምነት ተፈራረሙ::

 

ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ለመስራት ስምምነት ተፈራረመ፡፡ የፊርማ ስነ ስርዓቱን የፋና ብሮድካስቲን ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው እና የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አህመድ ተፈራርመዋል፡፡

በስሩ 35 ኩባንያችን ያቀፈው ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር የተፈራረመው በግሩፑ ስር ያሉ ኩባንያዎች የሚያከናውኗቸውን ዘርፈ ብዙ ተግባራት በፋና ሬዲዮና ቴሌቪዥን እንዲሁም በፋና ድረ-ገጽ አማካይነት ለህዝብ እንዲደርስ ለማድረግ መሆኑ ስምምነቱ በተፈረመበት ወቅት ተገልጿል፡፡

ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በውስጡ የነበሩትን የምርታማነትና የማኔጅመንት ችግሮች ለመፍታት ሰፊ ስራ ሲሰራ መቆየቱን የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አህመድ በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ ገልጸው፤ የሜዲያ አጠቃቀማችንን ማሻሻል አንዱ የሪፎርማችን አካል ነበር ብለዋል፡፡ ይህንንም ክፍተት ለመሙላት ከሁለት የሜዲያ ተቋማት ጋር አብሮ ለመስራት መወሰኑን የኢንቨስትመንት ግሩፑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አህመድ ተናግረዋል፡፡

ፋና የተመረጠበትን ምክንያት በተመለከተ አቶ ጀማል ሦስት ነጥቦችን ጠቅደሰዋል፡፡ ይኸውም፡- ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የሀገርን ልማት ለማፋጠንና የሀሪቱን እድገት ለማሳደግ እየሰራ ያለ ተቋም እንደመሆኑ የድርጅቱን ዓላማ የሚጋሩ አካላት ጋር አብሮ መስራት አስፈላጊ በመሆኑ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት መመረጡን ስራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ቋንቋዎች፣ በተለያዩ አማራጮች፣ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ተደራሽ መሆኑ ሌላው ተመራጭ የሆነበት ምክንያት ነው ብለዋል አቶ ጀማል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፤ ፋና የሚሰራቸው ዘገባዎች፣ ዜናዎችና ፕሮግራሞች የህዝብ የሆኑ እንዲሁም በስራዎቹም ኃላፊነት የሚሰማው ተቋም  በመሆኑ ፋናን ተመራጭ እንዳደረገው አቶ ጀማል አህመድ አስረድተዋል፡፡

 አቶ ጀማል ቀጥለውም “ከፋና ጋር የጋራ ግብ አለን፡፡ የጋራ ግባችን ሀገራችንን ማልማት ነው፡፡ በሀራችን ልማት የድርሻችንን ለመወጣት እንደ ፋና ካለ ኃላፊነት ከሚሰማው ሜዲያ ጋር አብሮ መስራት ለእውነትና ለሀቅ እንድንቆም ያደርገናል” ብለዋል፡፡

በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የፋና ብርድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው በበኩላቸው፤ ፋና በየእለቱ የህይወትን እንቅስቃሴ ከመዘገብ ባሻገር አብሮ የመስራትንና አንድ ላይ የመሻገርን መንገድ መምረጡን ገልጸው፣ “አገልግሎት ሰጪን እና አገልግሎት ፈላጊን የማገናኘት ስራ እንሰራለን” ብለዋል፡፡ በዚህ ረገድ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ህብረተሰብ ተኮር ስራ የሚሰራ በመሆኑ ምርትና አገልግሎቶቹን ለህብረተሰቡ በማድረስ ተያይዘን እናድጋለን ብለዋል፡፡ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ለህብረተሰብ ለውጥና ለሀገር እድገት ዘርፈ ብዙ ስራዎችን የሚሰራ ተቋም በመሆኑ እንደ ሚድሮክ ካደ ድርጅት ጋር በጋራ ለመስራት መስማማታቸው እንዳስደሰታቸው አቶ አድማሱ ተናግረዋል፡፡ሁለቱ ድርጅቶች ያደረጉት ስምምነት ለ52 ሣምንታት (ለአንድ ዓመት) የሚቆይ መሆኑ ታውቋል፡፡