ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለተፈናቀሉ ዜጎች ለእለት ቀለብ የሚሆን የዱቄት እርዳታ አደረገ፡፡ ይህንኑ እርዳታ ለማጓጓዝ አራት የጭነት መኪናዎች ታህሳስ 21 ቀን 2013 ዓ.ም ከአዲስ አበባ መንቀሳቀሳቸው ታውቋል፡፡

በቅርቡ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተከሰተው ሁከት ምክንያት በርካታ ዜጎች ቤት ንብረታቸው ወድሞ፣ ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው ለከፍተኛ እንግልት መዳረጋቸው ይታወቃል፡፡ የዜጎች መፈናቀልና ሞት አፋፍ ላይ መድረስ ያሳሰበው ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ለእለት ቀለብ የሚሆን አንድ ሺህ ሁለት መቶ ኩንታል ዱቄት በአራት የጭነት መኪናዎች ወደ ቡለን ወረዳ እንዲጓጓዝ ማድረጉ ታውቋል፡፡

ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን፣ በቡለን እና በጉባ ወረዳዎች የማዕድን ፕሮጄክቶች ያሉት ሲሆን፤ እነዚህም የወርቅ እና የእምነበረድ ፕሮጄክቶች ማንኩሽ፣ ሞራ እና ኢኮንቲ በሚባሉ አካባቢዎች ይገኛሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ንብረት የሆነው የጉባ እርሻም የሚገኘው በዚሁ ክልል መሆኑ የታወቃል፡፡