ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በ2013 በጀት ዓመት የተሻለ አፈፃፀም ላሳዩ ሰራተኞች እውቅናና ከ2.5 ሚሊየን ብር በላይ ሽልማት አበረከተ፡፡

የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አህመድ መድረኩን በንግግር ሲከፍቱ ዘርፉ ከአምና ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ እድገት ማሳየቱን ገልጸዋል፡፡

በግሩፑ ውስጥ ካሉ ድርጅቶች መካከል 17ቱን ያቀፈው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የ13ቱን ድርጅቶች እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ሀምሌ 27 ቀን 2013 ዓ.ም አቅርቧል፡፡

ሪፖርቱን ያቀረቡት የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አካለወልድ አድማሱ እንደተናገሩት በበጀት ዓመቱ ከ4 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላይ ተመርቷል፡፡ ይህም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ130 በመቶ ብልጫ ማሳየቱን አስረድተዋል፡፡

ሽልማቱን የሰጡት የግሩፑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አህመድ እንደገለጹት ኪሳራ ውስጥ የነበሩ ድርጅቶች ሰራተኞችን ስልጠና ሰጥቶና አወቃቀር አስተካክሎ በመሰራቱ አጥጋቢ ባይባልም ተስፋ ሰጪ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል፡፡ ለዚህም የዘርፉ ሰራተኞችንና በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችን አመስግነዋል፡፡በዘርፉ ከዚህ የተሸለ ለውጥ እንዳይመጣ ኪሳራ ውስጥ የነበሩ ከሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ የመጡ ድርጅቶች ሰራተኞችን በጫና ውስጥ ማሰራት አስቸጋሪ መሆኑ፣የኮቪድ 19 ወረርሽኝና የውጭ ምንዛሬ እጥረት ፈተናዎች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ለሠራተኞች የእውቅና ሽልማት መካሔዱ የግሩፑን አቅም ለማጎልበትና የሠራተኛውን ተነሳሽነት ለማሳደግ እንደሚያግዝ ነው አቶ ጀማል የገለፁት፡፡

በዘርፉ ለ5660 ዜጎች የሥራ እድል የተፈጠረ ሲሆን በዓመቱ ከፍተኛ አፈፃፀም ላስመዘገቡ ሠራተኞች እውቅናና የማበረታቻ ሽልማትም ተሰጥቷቸዋል፡፡

የሽልማቱ መልዕክት ሠራተኛው በጣረ ቁጥር የበለጠ ተጠቃሚ እንደሆነ ለመግለጽ ነው ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው በሚቀጥለው ዓመት ዘንድሮ ከተገኘው ከእጥፍ በላይ ለማግኘት እቅድ መያዙን ገልጸዋል፡፡

የእውቅና ሽልማት የተበረከተላቸው ሠራተኞች በበኩላቸው ሽልማቱ የበለጠ ለመሥራት የሚያነሳሳ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

ለሁሉም ተሸላሚዎች ከ2.5 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ተበርክቷል፡፡