ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ለአመራሮቹ “ስትራቴጂክ ማኔጅመንትና የሥራ አመራር ለውጥ ” ላይ ያተኮረ ሥልጠና መስጠት ጀመረ፡፡

በግሩፑ ውሥጥ ከሚገኙት ዘርፎች መካከል የእርሻ እና አግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ አመራሮች ከመስከረም 10 እስከ መስከረም 14/2014 ዓ.ም በቢሾፍቱ የተሰጣቸውን ሥልጠና አጠናቀዋል፡፡
ሥልጠናው ከኢትዮጵያ ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የተሰጠ ሲሆን በተለይም የስትራቴጂክ እቅድ አዘገጃጀትና የለውጥ ሂደት አመራር ላይ ያተኮረ ነበር፡፡
በዚህ ሥልጠና ላይ በዘርፉ ውስጥ ካሉ 12 ኩባንያዎችና 58 የእርሻ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች የተውጣጡ ከ50 በላይ አመራሮች ተሳትፈዋል፡፡
በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ከአንድ ዓመት በፊት በተደረገ የአመራርና አደረጃጀት ለውጥ በኋላ በሌሎች ዘርፎችም ይሁን በእርሻ እና አግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ ኪሳራ ውሥጥ የነበሩ ተቋማት ከፍተኛ የሚባል ትርፍ ማስመዝገብ ችለዋል፡፡የተመዘገበውን ለውጥ በተሻለ መንገድ ውጤታማ ለማድረግ ስልጠናው መዘጋጀቱንና ሁሉም ወደ ተቋሙ ሲመለስ ያገኘውን እውቀት እስከ ታችኛው እርከን እንዲያወርድ በግሩፑ የእርሻ እና አግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኢሳያስ ከበደ ተናግረዋል፡፡
በሥልጣናው መዝጊያ ላይ የተገኙት አቶ ኢሳያስ ለተሳታፊዎቹ የሥራ መመሪያም ሰጥተዋል፡፡
ሥልጠናው በቀጣይ ቀናትም በተመሳሳይ ርዕስ በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ሥር ላሉ ሌሎች ዘርፎች አመራሮች እንደሚሰጥም ይጠበቃል፡፡ በሰኢድ መሀመድ
በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ