ለ3ኛ ጊዜ በተካሄደው የአፍሪካ ካይዘን ፍልፍስፍና አተገባበር ውድድር የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ አካል የሆነው ሆራይዘን አዲስ ጎማ አሸነፈ፡፡

በታንዛንያ በተካሄደው ውድድር የካይዘን ፍልፍስፍና የተገበሩ ከ9 ሀገራት የተውጣጡ 16 ድርጅቶች ተሳትፈውበታል፡፡ውድድሩ የካይዘን ፍልፍስፍናን በመተግበር ጥራትና ምርታማነትን በማሻሻል አመርቂ ውጤት ያመጡ ተቋማትን እውቅና መስጠትን ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡በዚህ ውድድር ኢትዮጵያ ያቀረበቻቸው የሆራይዘን አዲስ ጎማ እና የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ የሀዋሳ ቅርንጫፍ የላቀ ውጤት በማምጣት አሸናፊ ሆነዋል፡፡ኢትዮጵያ የካይዘን አሰራረርን በመተግበር በርካታ ወጪ መቀነሷን የገለጹት የኢትዮጵያ ካይዘን ኢንስቲትዩት ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ አስናቀ ጉዲሳ ከጃፓን መንግስት ጋር በቅርበት በመስራት የልህቀት ማዕከል እየተገነባ ይገኛል ብለዋል፡፡በውድድሩም በአሸናፊነት ከተመረጡ 5 ድርጅቶች ውስጥ እጅግ የላቀና የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ የኢትዮጵያ ተቋማት ካይዘንን በመተግበራቸው ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው የገለጹት፡፡የሆራይዘን አዲስ ጎማ ማኔጅመንትን ወክለው በሥነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት አቶ ዳዊት ደምሌ እንደተናገሩት”በኢንስቲትዩቱና በጂአይካ ከተመረጥን በኋላ የሰራናቸው ሥራዎች ተጎብኝተውልናል፡፡በተደጋጋሚ ጊዜ በኦንላይን ‘ፕረዘንቴሽን’ አቅርበናል፤መረጃዎች ተለዋውጠናል፡፡ ዶክመንቶችንም አቅርበናል፡፡ምንም እንኳን የሰራነው ለሽልማት ሳይሆን ይጠቅመናል ብለን ቢሆንም ባስመዘገብነው ውጤትና ባገኘነው እውቅና ግን ደስተኞች ነን ፡፡ ” ብለዋል፡፡

Title