ሚድሮክ ጎልድ ኃ. የተ. የግል ማህበር እና ብሔራዊ የማዕድን ኮርፖሬሽን ኃ. የተ. የግል ማህበር ከኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ጋር ስምምነት ተፈራረሙ፡

የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ አባል ኩባንያ የሆኑት ሚድሮክ ጎልድ ኃ. የተ. የግል ማህበር እና ብሔራዊ የማዕድን ኮርፖሬሽን ኃ. የተ. የግል ማህበር ከኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ጋር ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

በኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ በኩል ስምምነቱን የፈረሙት ዳይሬክተሩ አቶ እንዳለው መኮንን ሲሆኑ፤ በሚድሮክ ጎልድ ኃ. የተ. የግል ማህበር በኩል ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ ቱሉ ለማ፣ በብሔራዊ የማዕድን ኮርፖሬሽን ኃ. የተ. የግል ማህበር በኩል ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ በየነ ጨመዳ ስምምነቱን ፈርመዋል፡፡

የስምምነቱ ዓላማ “ISO 9001፡2015” የተሰኘውን የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓትን (ISO 9001፡ 2015 Quality Management System -QMS) ተግባራዊ በማድረግ ሂደት ሊኖር የሚገባውን የቴክኒክ እገዛ በተመለከተ መሆኑ ታውቋል፡፡

የቴክኒክ እገዛው ተግባራዊ የሚሆነው የከፍተኛ አመራር ገለፃን፣ ሥልጠናን፣ ሂደቱን መለየትና መዘርዘር፤ እንዲሁም የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት ሰነድን እና የውስጥ ኦዲትን በሚሸፍን ፕሮጀክት መልክ ሲሆን፤ ሁለቱ ወገኖች በሚከተሉት ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ መስማማታቸው ተገልጿል፡፡

በስምምነት ሰነዱ ላይ እንደተገለጸው ለሚድሮክ ጎልድ ኃ. የተ. የግል ማህበር እና ለብሔራዊ የማዕድን ኮርፖሬሽን ኃ. የተ. የግል ማህበር የተሰጣቸው ኃላፊነት፡-

 • የአስተዳደር ተወካይ መመደብና የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት ትግበራ ቡድን ማቋቋም፣
 • የሥራ አመራር ስርዓቱን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የድርጊት መርሐ ግብር ማዘጋጀት እና የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት ትግበራ እቅድን አክብሮ መስራት፣
 • የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓትን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለማስፈጸም የሚያስችል ሀብት መመደብ፣ የአተገባበር ሂደቱን በየጊዜው መገምገም እና ተገቢ እርምጃዎችን በወቅቱ መውሰድ፣
  እንዲሁም በስምምነቱ መሰረት የአገልግሎት ክፍያዎችን መፈጸም የሚሉ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ኃላፊነቶች ደግሞ፡-

 • የጥራት ሥራ አመራር ስርዓት (ISO 9001: 2015) አተገባበርን የሚያግዝ ባለሙያ መመደብ፣
 • የጥራት ሥራ አመራር ስርዓትን መሰረታዊ መርሆዎች እና መስፈርቶችን በተመለከተ ለኩባንያዎቹ ከፍተኛ አመራሮች ማብራሪያ መስጠት፣
 • በስራ ላይ ባለው የኩባንያዎቹ የስራ አመራር ስርዓት ላይ የክፍተት ትንተና ማድረግ፣
 • በጥራት ሥራ አመራር ስርዓት ፅንሰ-ሀሳቦች፣ መስፈርቶች፣ የአተገባበር ፍኖተ ካርታ፣ የሰነዶች አደረጃጀት፣ አተገባበርና በውስጥ ኦዲት አፈጻጸም ዙሪያ ለጥራት ሥራ አመራር ስርዓት የትግበራ ቡድን አባላት ስልጠና ለመስጠት፣
 • ውጤታማ የጥራት ሥራ አመራር ስርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ የሚረዳ አስፈላጊውን የቴክኒክ ድጋፍ ማድረግ፣
  እንዲሁም የውስጥ ኦዲት በሚደረግበት ወቅት እገዛ ማድረግ የሚሉት ናቸው፡፡

“ISO 9001: 2015” ለጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት (Quality Management System -QMS) የተሰጠ ዓለም አቀፍ ደረጃ ሲሆን፤ በየትኛውም ጂኦግራፊያዊ አካባቢ፣ በማንኛውም ድርጅት፣ በየትኛውም የንግድ ዘርፍ ተፈፃሚነት ያለው ዓለም አቀፍ ስምምነት ነው፡፡

“ISO 9001፡2015” የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት፤ የደንበኞችን እርካታ እና የድርጅታዊ ውጤታማነትን ግብ የሚደግፉ ሂደቶች፣ ሀብቶች እና ባህላዊ እሴቶች ድምር ውጤት ነው።